Gemini_Generated_Image_8wy6dg8wy6dg8wy6

ኮሚሽኑ የልማትና የመንፈሳዊ አገልግሎቶችን ለማቀናጀት በተዘጋጀው ስልታዊ ዕቅድና ተቋማዊየሪፎርምማዕቀፎች ላይ አውደ-ጥናት አደረገ

ሆሳዕና፡-የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን የሰብአዊ ድጋፍ እና ልማት ኮሚሽን በ10 ዓመት ስልታዊ አቅጣጫ እና በ5 ዓመት ስልታዊ ዕቅድ፣በቅንጅታዊ አሰራር ማዕቀፍ፣የአደጋ ሥጋት ቅደመ-ዝግጅት(ሀብት አሰባሰብና አመራር)፣መንፈሳዊና ሰብዓዊ/ልማትን ለመቀናጀት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቶች እና የቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን ተሞክሮን በተመለከተ ከቀጣናዎች በተወጣጡ የየዘርፉ መሪዎች በሆሳዕና እናት ቃለ ሕይወት አጥቢያ ቤተክርስቲያን የምክክርና አወደ-ጥናት ከሀምሌ17-18/2018 ዓ.ም አካሄዷል፡፡

በምክክሩ የኮሚሽኑ ቦርድ ሳብሳቢና የኢ/ቃ/ሕ/ቤ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ዳንኤል ጫዕሜቦ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶ/ር ተፈራ ተሎሬ ፣ ምክትል ኮሚሽነር ዶ/ር ወይታ ወዛ ፣ ዶ/ር ኢንጂነር ንጋቱ ጫፎ ፣ አቶ አብርሃም አላምቦ፣የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ሥራ አስፈጻሚ አባል እና በክላስተር ቀጣናዎች የቦርድ አባላት የሴቶች የወጣቶች እና የየቀጣና የልማት አስተባባሪዎች ተሳታፈዋል።

የኮሚሽኑ ቦርድ ሳብሳቢና የኢ/ቃ/ሕ/ቤ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ዳንኤል ጫዕሜቦ እንደገለጹት፤ ይህ ተቋማዊ ሪፎርም በሰው ኃይል እና በአሠራር ተቋሙን በማነጽ ለለውጥ እና ለአዲስ ዘመን በሚመጥን መልኩ የማኔጅመንት እና የትግበራ ሥራዎችን ለማከናወን ያለመ ነው። በተለይም የሰው ኃይልን በእውቀት፣ በክህሎት፣ በአስተሳሰብ እና በተግባር በማበልጸግ የአዕምሮ ውቅር ግንባታ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው፡፡ ለዚህም የሚያስችሉ መዋቅሮችን የማሻሻል፣ የማሳለጥ እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዲጂታል አገልግሎት የመስጠት ሥራዎች እንደ ቀዳሚ ግብ ተይዘው እየተሰራበት መሆኑን ገልጸው ሌላኛው ዋናው አቅጣጫ ደግሞ የቤተ ክርስቲያኒቱን መንፈሳዊ አግልግሎት እና  የልማት ሥራን ማቀናጀት እንደሆነ አመለክተዋል። ይህ የቅንጅታዊ አሰራር ማዕቀፍ በቀደሙ ቦርድ አመራር የጸደቀ ሲሆን፣ አሁን ላይ ማዕቀፉን ተግበራዊ ለመድረግ እየተሰራ መሆኑን  አቶ ዳንኤል ተናግረዋል።

በእነዚህ መድረኮች ከተሳተፉ የቀጠና ሰብሳቢዎች፣ ዋና ጸሐፊዎች፣ የልማት ፕሮጀክት አስተባባሪዎች እና የልማት ቦርድ አባላት የተገኘው ግብረ-መልስ፤ አብያተ ክርስቲያናት በአካባቢያቸው ያለውን ሀብት ማሰባሰብ እንዳለባቸው የሚያነሳሳ እና የቅንጅት አሠራሩን ተግባራዊ ለማድረግ መንገድ የከፈተ መሆኑ ተጠቅሷል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶር ተፈራ ተሎሬ ኮሚሽኑ የ10 ዓመት ስልታዊ አቅጣጫ እና የ5 ዓመት ስልታዊ ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ስራ መግባቱ ገልጽው በአውደ ጥናቱ ለተገኙት የተለያዮ ቀጠና መሪዎችም የኮሚሽኑን የ10 ዓመት ስልታዊ አቅጣጫ እና የ5 ዓመቱን ዕቅድ በተመለከተ ሰፍ ያለ ማብራሪያ አደርገዋል፡፡

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ዶክተር ወይታ ወዛ በበኩላቸውም ስለ ቅንጅታዊ አሰራር ማንዋል ለአወደ-ጥናት ተሳታፊዎች ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ቃለ-ሕይወት ቤተክርስቲያን አሁን በዚህን ጊዜ ነቅታ ወደ ቅንጅታዊ አሰራር መምጣት ለቤተክርሲቲያኒቱ ሁለንተናዊ አገልግሎት አስፈላጊ እንደሆነ እና ከሁሉም በላይ ደግሞ ቅንጅታዊ አሰራርን የእግዚአብሔር ቃል መርሆች መመሪያ በማደረግ መታዘዝ አለብን የሚል አቋም መያዙን ገልጸዋል።

የኮሚሽኑ የቦርድ አባል የሆኑት ዶክተር ጌታቸው በገና እንደተናገሩት፤ ይህ የምክክር መድረክ ቤተ ክርስቲያኗ ሰዎችን በመንፈሳዊውም ሆነ በልማቱ ዘርፍ በተቀናጀ መልኩ ለማገልገል የሚታደርገውን ጥረት የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸው ይህ አሠራር የአንድ አካል ብቻ ሳይሆን የሁሉም ምዕመናን እና የክርስቲያኖች ድርሻ መሆኑን በመጠቆም፤ እያንዳንዱ አባል በተሰጠው የጸጋ ስጦታ በገንዘብ፣ በማስተማር፣ በማስተዳደር እና በምስክርነት እንዲያገለግል ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን በደቡብ  ሸዋ ቀጠና የቀጠናው ሰብሳቢ ደስአለኝ ግርማ እንደገለጹት፤ ሥልጠናው በዋናነት የሚያተኩረው የልማት ኮሚሽኑ ከቤተክርስቲያኒቱ መዋቅር ጋር በቅንጅት የሚሠራበትን፣ ዕቅዶችን እስከ ታችኛው መዋቅር የማውረድ እና የታለሙትን ግቦች የማሳካት ሁኔታዎች ላይ ነው።

ይህ የቅንጅት አሠራር እሳቤ በጠቅላላ ጉባኤው ጸድቆ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ የሰፈረ ሲሆን፤ የአሁኑ ሥልጠናም ከተለያዩ ቀጠናዎች ለተወጣጡ መሪዎች እና ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ለማስጨበጥ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን የሰብዓዊ ድጋፍ እና ልማት ኮሚሽን ያዘጋጀው የስልታዊ ዕቅድና ማቀናጀት ሥልጠና በትክክለኛ ጊዜ የተሰጠ እና ወደ ተግባር ለመግባት የሚያነሳሳ መሆኑን የደቡብ ምሥራቅ ሸዋ ቀጠና ዋና ጸሐፊ አገልጋይ በላቸው ዴታሞ ገለጸው ቤተ-ክርስቲያኗ 100ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሏን ለማከብር በዝግጅት ላይ ባለችበት በዚህ ወቅት፣ በልማት አገልግሎት ያለፈችበትን ሂደት በመገምገምና ክፍተቶችን በመሙላት አዲስ መነቃቃት መፈጠሩ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው። ሥልጠናው አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በትክክል ያሳየ እና ወደፊት የሚኬድበትን አቅጣጫ በግልጽ ያስቀመጠ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።

በቀጠናው ደረጃ ከሥልጠናው ማጠቃለያ በኋላ ጠንከር ያለ ውይይት በማድረግ፣ የተገኘውን ግንዛቤ ከመግለጫና ባለፈ መሬት የረገጠ ተግባራዊ ሥራ ላይ ለማዋል እና የቅንጅት አሠራሩን ለማስቀጠል ቀጠናው ዝግጁ መሆኑን እና ቃል መግበታቸውን አስታውቀዋል።

በመጨረሻም ይህ አሠራር ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን በቀጠና፣ በኅብረት እና በአጥቢያ ደረጃ ያሉ መዋቅሮች ተቀናጅተው እንዲሠሩ፣ የአጥቢያዎችን አቅም በመገንባት፣ አሠራሮችን በመዘርጋት እና በማደራጀት የልማት ሥራዎችን የበለጠ አጠናክሮ ለመቀጠል አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ተብራርቷል። በአሁኑ ወቅትም ተመሳሰይ አውደ ጥናት በጅማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *