7G0A0574

ኮሚሽኑ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን የቤት ውስጥ ውሃ ማጣሪያ (BSF) ፕሮጀክት ይፋ አደረገ

ወልቂጤ፡ ነሐሴ 14/2018 ዓ.ም. — የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን የሰብአዊ ድጋፍ እና ልማት ኮሚሽን (ኢቃሕቤ-ሳድልኮ) ከሳማሪታንስ ፐርስ ካናዳ (Samaritan’s Purse Canada) ጋር በመተባበር በ54 ሚሊዮን ብር በጀት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን 5,000 አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የባዮ-ሳንድ ፊልተር (BSF) የውሃ ማጣሪያ ፕሮጀክትን በይፋ አስጀምሯል።

ይህ ለአንድ ዓመት የሚቆይ የፓይለት ፕሮጀክት በሳማሪታንስ ፐርስ ካናዳ በተገኘ የ54 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ የሚከናወን ሲሆን፤ በጉራጌ ዞን በሚገኙ አራት በተመረጡ ወረዳዎች ውስጥ እንደሚተገበር በኮሚሽኑ የዋሽ ክፍል ፕሮግራም ኃላፊ አቶ ቸርነት ብርሃኑ ገልጸዋል።

ይህ ፕሮጀክት ትላልቅ የውሃ መሰረተ ልማቶች ለሌላቸው ለገጠር አባወራዎች የተነደፈ እጅግ ወጪ ቆጣቢ የሆነ የውሃ ማከሚያ ቴክኖሎጂን የሚያቀርብ ፕሮጀክት ነው፡፡ ህብረተሰቡ ያልተጣራ ውሃ ከምንጮችን ወይም ከወንዞች  ከከብቶች ጋር ተጋርቶ ለመጠቀም በሚገደድበት ሁኔታ ላይ የሚፈጠሩ የውሃ መበከል ችግሮችን የሚቀርፍ መሆኑን አቶ ቸርነት ገልጸው፤ ያልተጣራ ውሃን በቀጥታ በቤት ውስጥ በማጣራት ባዮ-ሳንድ ቴክኖሎጂው ለአገልግሎት የሚሆን ንጹህ የመጠጥ ውሃ ወዲያውኑ ማግኘት እንዲችሉ ያስችላል ብለዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የውሃ፣ መስኖ እና ማዕድን ቢሮ ኃላፊ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አቶ ሀይሌ ደዊ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን ለክልሉ ዋና የልማት አጋር ሆና ማገልገሏን ቀጥላለች ብለዋል። ይህ ጥረት ለንጹህ ውሃ ማጣሪያ ወቅታዊና አሰፈላጊ ፕሮጀክት ሲሆን፤ የማህበረሰቡን ጤና እና የዕለት ተዕለት የአኗኗር ዘይቤ በቀጥታ ያሻሽላል ሲሉ ገልጸዋል።

የክልሉ አስተዳደር ለፕሮጀክቱ ስኬት ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ያረጋገጡት አቶ ሀይሌ ደዊ፤ የክልሉ ባለሥልጣናት ከዞን እና ከወረዳ አመራሮች ጋር በመቀናጀት የተቀናጀ ቁጥጥር እና ውጤታማ ትግበራ እንዲኖር አብረው እንደሚሰሩ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ይህ ፕሮጀክት የንጹህ ውሃ መሰረተ ልማት የሌላቸውን እና በቀጥታ በወንዝ እና በምንጮ ውሃ ላይ ጥገኛ የሆኑ ማህበረሰቦችን ታላሚ ያደረገ በመሆኑ በውሃ ወለድ በሽታዎች እና ተያያዥ የጤና እክሎች የሚመጡ ችግሮችን ይቀንሳል ሲሉ የጉራጌ ዞን ውሃ፣ ማዕድን እና ኢነርጂ መመሪያ ኃላፊ አቶ አየለ ፈቀደ ገልጸዋል።

አቶ አየለ አክለውም ኮሚሽኑ ጋር ያለውን የረጅም ጊዜ አጋርነት አጉልተው ያሳዩ ሲሆን፤ ቀደም ሲል በአረቅት፣ እንደጋኝ፣ አበሽጌ፣ ጉመር እና ቸሃ ወረዳዎች በውሃ አቅርቦት ግንባታ፣ በሳኒቴሽን እና ሃይጂን ማስተዋወቅ እንዲሁም በወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ ላይ የተከናወኑ ስኬታማ ሥራዎችን አውስተዋል።

በፕሮጀክቱ ማስጀመር ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የማሀል ሻዋ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን  ዋና ጸሐፊ አቶ ደንድር በሰር፤ ይህ ፕሮጀክት በአካባቢው ህብረተሰብ ዘንድ ያለውን የንጹህ ውሃ ችግር በቀጥታ እንደሚቀርፍ ተናግረዋል።

ማህበራዊ አገልግሎቶችን ከአጠቃላይ የልማት ሥራዎች ጋር ማቀናጀት ከቤተክርስቲያኗ ዋና ተልዕኮ ጋር የሚጣጣምና የወንጌል አገልግሎትን ለማስፋፋት ትልቅ በር የሚከፍት መሆኑን ጠቁመዋል። በመሆኑም የማሀል ሻዋ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን በዞኑ ይፋ የተደረገውን አዲስ የባዮሳንድ ፊልተር (BSF) የውሃ ፕሮጀክት ትግበራ ለማገዝ ሙሉ ቁርጠኝነቷን በይፋ አረጋግጣለች።

ባለፉት አምስት አስርት ዓመታት ኮሚሽኑ በሀገራዊ የድህነት ቅነሳ ጥረቶች ውስጥ መሪ ሚና በመጫወት የአስቾኳይ ጊዜ እርዳታና መልሶ ማቋቋም፣ በጤና፣ በግብርና፣ በትምህርት ቤት ምግብ አቅርቦት፣ በሰላም ግንባታ እና በራስ አገዝ ቡድኖች የኢንተርፕራይዝ ማጠናከር ላይ ሕይወትን የሚቀይሩ ተግባራትን አከናውኗል።

በኮሚሽኑ የክትትልና ግምገማ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ኪዳን ቴኒ በበኩላቸው እርዳታ ብቻውን በቂ አይደለም፤ እውነተኛ ልማት የሚመጣው እያንዳንዱ ጣልቃ ገብነት ዘላቂና አወንታዊ ተጽእኖ እንዲኖረው የአካባቢውን ማህበረሰብ በማብቃት እና ዝግጁ በማድረግ ነው ሲሉ ገልጸዋል። በዚህ አከባብ እ.ኤ.አ. ከ2022 እስከ 2025 ባሉት ዓመታት ውስጥ ብቻ በ3 ወረዳዎች እና በ20 ቀበሌዎች ከ100 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር በላይ ፈሰስ ተደርጓል። በእነዚህ ሥራዎች ውስጥ የእኛ ዋና ትኩረት የማህበረሰቡን ባለቤትነት ማረጋገጥ፣ የአካባቢውን አቅም መገንባት እና ዘላቂነትን ለማረጋገጥ አቅም ያላቸው ተቋማት ጋር ጠንካራ ትስስር መፍጠር ነው።

በዚህ ቀን ይህን የባዮሳንድ ፊልተር (BSF) ፕሮጀክትን ኮሚሽኑ በይፋ መጀመሩን የገለጹት አቶ ክዳን ይህ በአራት ወረዳዎች ለአንድ ዓመት የሚቆይ የፓይለት ፕሮጀክት ነው፡፡ ለ5000 ሺህዎች ቤተሰቦች ዘላቂ የሆነ የቤት ውስጥ ንጹህ የመጠጥ ውሃ  ለማቅረብ አይነተኛ ሚና ይጨወታል፡፡

Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *