ዶ/ር ተፈራ ታሎሬ የኢትዮጰያ ቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን ሰብዓዊ ድጋፍና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት ድርጅቱ በኢትዮጵያዊያን አቆጣጠር ከሃምሳ አንድ ዓመት በፊት በ1966 ዓ.ም በወሎ በተከሰተው ድርቅና ርሃብ ምክንያት እርዳታ በማድረግ ስራ መጀመሩን ገልጸው በዋናነት በትምህርት፣በሰላም ግንባታ፣በሰብዓዊ ድጋፍ እና ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ በሃገሪቱ አንድ መቶ አርባ (140) ፕሮጀክቶች ስራ ላይ መሆናቸውን ገለጸው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከሪፖርት በተጨማሪ በአካል የድርጅቱን ስራ ለመመልከት በመገኘቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የቲር ፈንድ የኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ Simba Gorden Nyamarezi በበኩላቸው የተሻለ ልማትና ውጤት ማምጣት የሚቻለው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅትና በትብብር መስራት ሲቻል መሆኑን ጠቅሰው ከባለስልጣን መስሪያቤቱ ጋር የጀመርነውን ትስስር አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በድሬደዋ ፣ምዕራብ ሃረርጌ እና በጂግጂጋ ድርጅቱ የሰራቸውን ስራዎች በሪፖርት የቀረበ ሲሆን በጉብኝቱም በርካታ ሰው ተኮር ስራዎች መሰራታቸውን መመልከት ተችሏል፡፡
የድሬደዋ ከተማ የቃለህይወት የልጆችና ወጣቶች የልማት ፕሮጀክት በአስር ዓመታት ቆይታው በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን የጠቀሱት የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ታደሰ ቢረዳ ዝቅተኛ የኑሮ ጀረጃ ላይ ለሚገኙ ዘጠኝ መቶ አስራ ስምት ልጆች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ድርጅቱ ከኬጂ ጀምሮ አሁን ላይ በዩኒቨርሲቲ የሚያስተምራቸው ልጆች መኖራቸውን አብራርተው ከዚህ በተጨማሪ ለልጆቹ የህክምና ፣ የምግብ ቁሳቁስ ፣ የትምህርት ቤት ግብዓቶችን በሟሟላት እና ለወላጆች በኢኮኖሚ እራሳቸውን እንዲችሉ ለስልሳ ወላጆች የተለያዩ የሙያ ስልጠና መስጠቱን አብራርተዋል፡፡
በባለፉት አስር ዓመታት አንድ መቶ ሃያ ስድስት ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን በመግለጽ ፕሮጀክቱ የልጆች ስነምግባር ፣አካላዊ እና ማህበራዊ ዕድገት ፣በትምህርት እና አስተዳደራዊ ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
ህጻናቱ በሰጡት አስተያየትም ድርጅቱ እርዳታ ባያደርግላቸው የዕለት ጉርስ ፍለጋ ከትምህርታቸው ሊስተጓጎሉ ይችሉ እደነበር ገልጸው ቃለ ህይወት የእርዳታ ኮሚሽንን ስለሚያደርግላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በተመሳሳይ ሐረር ሚደጋ ቶላ ላይ ሃምሳ አምስት ሺህ (55000) የማህበረሰብ ክፍሎችን ተደራሽ የሚያደርግ እና በሶስት ዓመት የሚጠናቀቅ ፕሮጀክት መኖሩን የገለጹት የፕሮግራሙ አስተባባሪና ሃላፊ አቶ አላዩ መኩሪያ ይህንን ተፈጻሚ ለማድረግ ከሶስት ነጥብ አራት ሚሊየን ይሮ በላይ መመደቡን ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ የፕሮጀክቱ ሃምሳ ፐርሰንት መጠናቀቁን ገልጸው ከዚህ ፕሮጀክት ውስጥ በምዕራብ ሃረርጌ ሚደጋ ቶላ ኡርጂ ሌንጫ ቀበሌ ከሱማሌ ክልል ለተፈናቀሉ እና በድርቅ ለተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና እንስሳት መልሶ ማቋቋም ስራ እየተሰራ ሲሆን በዋናነት የውሃ ቦኖዎችን በመጠገን፣የገንዘብ ቁጠባን በማስተማር፣የውሃ ጉድጓድ በመቆፈር፣ለትምህርት ቤቶች መጸዳጃ ቤቶችን በመገንባት፣ምርጥ ዘር አቅርቦትና ለእርባታ የሚሆኑ ፍየሎችን እስከ መኖ የመስጠት ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የኡርጂ ሌንጫ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አስከ ሶስት መቶ ሃምሳ ሜትር ጥልቀት የሚቆፈር ሲሆን ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ሶስት ቀበሌዎችን የውሃ ችግር እንደሚቀርፍ ተገልጿል፡፡ በሌሎች ቀበሌዎችም መሰረታዊ የህዝቡ ችግር ውሃ በመሆኑ ይህንን ለመቅረፍ አገልግሎት መስጠት ያቆሙ የውሃ ቦኖዎችን በመጠገን ከሃያ አራት ሺህ በላይ የአከባቢውን ነዋሪዎች ችግር መፍታቱን መመልከት ተችሏል፡፡

ድርጅቱ በሚደጋ ቶላ የእርሻ እቀባ የሚባል አዲስ ቴክኖሎጂን ለመጀመሪያ ግዜ በማስተዋወቅ የገበሬውን ምርትና ምርታማነታቸው እንዲጨምር በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻላቸውን ገልጸው ከእርሻ ጎን ለጎን ለስድስት መቶ አርባ አራት አባወራዎች በድምሩ ሶስት ሺህ ሁለት መቶ ሃያ ፍየሎችን እስከነ መኖአቸው በመስጠት ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል፡፡










ሴቶች ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊት እንዲቆጠቡ እና በኢኮኖሚ እራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን በመስጠት ሁለት መቶ ሰማንያ ስምንት ሴቶችን በአራት ማህበር በማደራጀት ቁጠባ እንዲጀምሩ ማድረግ እና የንጽህና አጠባበቅ ስልጠናን መሰረት ያደረገ ለአንድ ሺህ አራት መቶ አርባ እማወራዎች የውሃ ማጣሪያ ለግሷል፡፡
በአከባቢው ሰልጠናውን ያገኙ እና የቁጠባ አባል የሆኑት ወ/ሮ ከድጃ ኢብራሒም እንደገለጹት ድርጅቱ በሰጠን ስልጠና እዚህ አከባቢ የነበርን ሴቶች ከጨለማ ወደ ብርሃን መጠናል፤ መብታችንን በደንብ አውቀናል፤ ሴቶች ልጆቻችንን ያለእድሜ እንዳይዳሩ እንከላከላለን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ተላቀናል በተለይም በየሳምንቱ በምናደርገው ውይይት የማህበራዊ ህይወታችን ላይ ትልቅ ለውጥ ነው ያመጣልን ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት ድርጅቱ የማህበረሰቡ የሁልግዜ ጥያቄ የሆነውን የውሃ ችግር ለመቅረፍ የሰራቸው ስራዎች በጣም አበረታች መሆኑን ገልጸው ፍላጎቱ ከፍተኛ በመሆኑ በሌሎች አከባቢዎችም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋ፡፡

Add a Comment