ኮሚሽኑ ሲያካሄድ የነበረውን ስልታዊ ዕቅድ፣ ቅንጂታዊ አሰራርና ተቋሟዊ የሪፎርም ማዕቀፎች አውደ-ጥናት አጠናቀቀ

አዲስ አበባ ፡-የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን የሰብዓዊ ድጋፍ እና ልማት ኮሚሽን(ኢቃሕቤ-ሳድልኮ) በለፉት ጊዜያት በአርባምንጭ፣ሀዋሳ፣ሆሳዕና እና ጅማ ለሚገኙ ለኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት አጥቢያ ቤተክርስቲያን ለቀጣና እና ኀብረት መሪዎች ሲሰጥ የቆየው ልማትና የመንፈሳዊ አገልግሎቶችን ለማቀናጀት በተዘጋጀው ስልታዊ ዕቅድና ተቋሟዊ የሪፎርም ማዕቀፎች ላይ በአዲስ አበባ ለቤተክርስቲያን እና በቤተክርስቲያኒቱ መዋቅር ከሚገኙ መሪዎች ጋር በማድረግ አወደ-ጥናቱን በስኬት አጠናቀቀ፡፡

አውደ ጥናቱ ከነሐሴ 8-9/2018 ዓ.ም  የተደረገ ሲሆን በዚህን ጊዜም በኮሚሽኑ የ10 ዓመት ስልታዊ አቅጣጫ እና በ5 ዓመት ስልታዊ ዕቅድ፣በቅንጅታዊ አሰራር ማዕቀፍ፣የአደጋ ሥጋት ቅደመ-ዝግጅት፣መንፈሳዊና ሰብዓዊ/ልማትን ለመቀናጀት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠርቶች እና የቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን ተሞክሮን በተመለከተ ከአጥቢያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን፣ከቀጣናዎች እና ኀብረት ለመጡ የየዘርፉ መሪዎች ጋር በአድስ አበባ የምክክርና አውደ-ጥናት ተደርጓል፡፡

በአውደ-ጥናቱ ከወለጋ፣ወሎሶ፣ባህር ዳር፣መቐለ፣ደሴ፣ድሬዳዋ፣አድስ አበባ ዋና ጽ/ቤት፣የአዲስ አበባና አከባቢዋ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን ቀጠና እና ኮሚሽኑ መኔጅመንት እና ቦርድ አባላት ተሳትፈዋል፡፡

እንዲሁም በአውደ-ጥናቱ የኮሚሽኑ ቦርድ ሳብሳቢና የኢ/ቃ/ሕ/ቤ/ያን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ዳንኤል ጫዕሜቦ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶ/ር ተፈራ ተሎረ ፣ ምክትል ኮሚሽነር ዶ/ር ወይታ ወዛ ፣ ዶ/ር ኢንጂነር ንጋቱ ጫፎ፣ አቶ አብርሃም አላምቦ፣የቦርድ አባላት፣ የሴቶች፣ የወጣቶችና መሪዎችና የልማት አስተባባሪዎች ተሳታፈዋል።

የኮሚሽኑ ቦርድ ሳብሳቢና የቤተክርስቲያኒቱ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ዳንኤል ጫዕሜቦ እንደገለጹት፤የልማት ህልውና ያለው በቤተክርስቲያን መኖር ነው፡፡ የቤተክርስቲያኒቱ ልማት ያለው ቤተክርስቲያን ስላለች ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ዘመን የቤተክርስቲያን መሪዎች የመንፈሳዊ አገልግሎትን እና ልማትን አቀናጅተው በመስራት እንደ ቀደሙት የቤተክርስቲያን መሪዎች ምሳሌ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

 በመቀጠልም እንደ ቤተክርስቲያን ማህበራዊ፣መንፈሳዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ በምድረቱ በማምጣት መገለጥ አለባት ምክንያቱም አውደ ጥናቱ ቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ አገልግሎቷን በተቀናጀ መንገድ እንድትፈጽም የሚያግዝ በመሆኑ እና ያላትን ሀብት በመለየት፣ በማደራጀትና በማልማት ለወንጌል መስፋትና ለሰው ልጅ ደህንነት እንድታውለው ሁነኛ መሳሪያ ነው።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር ተፈራ ተሎሬ ኮሚሽኑ የ10 ዓመት ስልታዊ አቅጣጫ እና የ5 ዓመት ስልታዊ ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል። አያይዘውም በበጎ አድራጎትና ልማት ዙሪያ ለተሰበሰቡት የየቀጠናው ሕብረት መሪዎች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በሌላ በኩል የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ዶክተር ወይታ ወዛ ቅንጅታዊ አሰራርን የሚያስረዳ መመሪያ ለአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች አስተዋውቀዋል። በገለጻቸውም የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን ለአጠቃላይ አገልግሎቷ ስኬት አሁን ላይ ቅንጅታዊ አሰራርን መከተል እንደሚያስፈልጋት በመጠቆም፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መርሆችም ለዚህ አሰራር መመሪያ እንደሚሆኑ እና ለእግዚአብሔር ቃል መታዘዝ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የአደጋ ጊዜ እርዳታ እና ሰብዓዊ ድጋፍ ፕሮግራም ማናጀር አቶ አብርሃም አለምቦ ደግሞ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሀብት እጥረት ሳይሆን የአስተሳሰብ ክፍተት እንደሚታይ ጠቁመው፣ የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በመሆኑም የውስጥ ሀብትን በእውቀትና በዕቅድ በመለየት፣ በማደራጀትና በማልማት መጠቀም ለቤተክርስቲያኒቷ አገልግሎት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

ሌሎች በአውደ ጥናቱ መድረክ የተሳተፉ መሪዎችም ስልጠናው መንፈሳዊ አገልግሎትና ልማትን አጣጥሞ ለመምራት የሚያስችል የአሰራር ማዕቀፍ በተመለከተ ግንዛቤ ያገኙበት እና ያለውን ሀብት በማወቅ መጠቀም እንደምቻል መንገድ ያሳየ “ዓይን ገላጭ” መድረክ እንደነበር ገልጸዋል።

በመጨረሻም ይህ ቅንጅታዊ አሠራር በተግባር እንዲረጋገጥ በቀጠና፣ በኅብረትና በአጥቢያ ደረጃ ያሉ መዋቅሮች ተቀናጅተው እንዲሠሩ፣ አቅማቸው እንዲገነባና የአሰራር ስርአቶች እንዲዘረጉ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል። ከተሳታፊዎች የተገኘው ግብረ-መልስ እንደሚያሳየው፣ አውደ ጥናቱ በአካባቢያቸው ያለውን የሀብት አቅም በመለየት አሰራሩን ወደ ተግባር ለመለወጥ ትልቅ መንገድ የከፈተ ሆኗል።